የኢንባንክ መ ዩ በሲቢኢ

 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ጋር በሲቢኢ ብር የዲጂታል ቁጠባ እና ብድር አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራረመ።
​ወርሃዊ ደሞዛቸውን በሲቢኢ ብር አማካኝነት የሚቀበሉ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ሠራተኞች እና መምህራን በ"ሲቢኢ በጅ" አማካኝነት የብድርና ቁጠባ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ስምምነት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በመቐለ ዩኒቨርሲቲ መካከል ተፈርሟል።

 የኢንባንክ መ ዩ በሲቢኢ
​ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቐለ ዲስትሪክት ተ/ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ታደሰ እና የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዓብደልቃድር ከድር ናቸው።
​የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቐለ ዲስትሪክት ተ/ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ታደሰ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ መቐለ ዩኒቨርሲቲ በውስጡ በርካታ እሴቶች እና ጠንካራ አቅም ያለው አንጋፋ ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ ባንኩ ተግባራዊ ለሚያደርጋቸው አዳዲስ እና ነባር የባንክ አገልግሎቶች በሁሉም ካምፓሶች የሚገኙ የአስተዳደር ሠራተኞች እና መምህራን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል። ከዚህ በተጨማሪም በዛሬው ዕለት በተፈራረምነው የመግባቢያ ሰነድ መሠረት ሠራተኞች የዲጂታል ብድር እና ቁጠባ ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።
​የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዓብደልቃድር ከድር በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ሠራተኞች እና ካምፓሶች ያሉት መሆኑን ገልጸው፣ የብድር አቅርቦቱ እና የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቱ የሠራተኞችን የኢኮኖሚ ፍላጎት የሚፈታ መሆኑን ተናግረዋል። ዶ/ር ዓብደልቃድር እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሠራተኞች የሚያስፈልገውን ድጋፍ እና የብድር አቅርቦት አጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነታቸው መሆኑን ገልጸው፣ ዩኒቨርሲቲውም ለባንኩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
​በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቐለ ዲስትሪክት የፋሲሊቲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓወት ፍሰሃየ፣ የአሪድ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ሃደራ እና ሌሎች የዲስትሪክቱ የሥራ አመራሮች ተገኝተዋል። ከዩኒቨርሲቲው በኩል ደግሞ የአስተዳደር እና ልማት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተከስተ ብርሃኑ፣ የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አታኽልቲ አዱኛ እና የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል።

Related Articles